.
Home አጠቃላይ ምርጫ ቦርድ ነጥብ ጥሏል፡ በጃዋር ጉዳይ እጁን ተጠመዘዘ ይሆን? || ተክለሚካኤል አበበ...

ምርጫ ቦርድ ነጥብ ጥሏል፡ በጃዋር ጉዳይ እጁን ተጠመዘዘ ይሆን? || ተክለሚካኤል አበበ ቶሮንቶ (ካናዳ)

ምርጫ ቦርድ ነጥብ ጥሏል፡ በጃዋር ጉዳይ እጁን ተጠመዘዘ ይሆን? || ተክለሚካኤል አበበ ቶሮንቶ (ካናዳ)

0
605

(ክፍል አንድ)

እንደመግቢያ፤

1-  ይህንን ጽሁፍ ከመቋጨቴ በፊት፤ ምርጫ ቦርድ ከጃዋር መሀመድ ጋር በተያያዘ የሰጠው ብይን እንዳለ ፈለግኩ፤ ምንም አላገኘሁም፡፡ ምርጫ ቦርድ በመረራ ጉዲና ለሚመራው ኦፌኮ፤ የጃዋርን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ማረጋገጫ ወረቀት እንዲያቀርብ የሰጠው የ10 ቀን ገደብ ቢያልፍም፤ ቦርዱ በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምንም ይፋዊ ብያኔ አልሰጠም፡፡ ቦርዱ፤ ምን ሊል እንደሚችልም እንጃ፡፡ ምናልባት ‹‹‹የጃዋርን የኦፌኮ አባልነት አንቀበልም፤ በዚህም መሰረት ለቀጣይ ምርጫዎች በእጩነት ሊቀርብ አይችልም››› ይል እንደሆን እንጂ፤ መቼም በዚህ የተነሳ የኦፌኮን ፈቃድ ሊሰርዝ አይሞክርም፡፡ ጃዋር ደግሞ፤ ምርጫ ቦርድ ተቀበለው አልተቀበለው፤ የፖለቲካ ተሳትፎውን አይገታውም፡፡ ቀድሞውንም ነገር ምርጫ ቦርድ ከጃዋር ጋር በተያያዘ የመጣበት መንግድ ስህተት ነው፡፡

2-  ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ከጃዋር ዜግነትና ኦፌኮ አባልነት ጋር በተያያዘ፤ ቦርዱና ድርጅቱ ኦፌኮ፤ ወይም ጃዋር የገቡትን እሰጥ አገባ በተመለከተ ስትጠየቅ የምትሰጠው መልስ፤ የገባችበትን አስቸጋሪ የፖለቲካ ቅርቃር እንዳልተረዳችና የያዘችው ሀላፊነት፤ ብልጠት፤ ብልሀት፤ ትእግስት፤ አርቆ አሳቢነት፤ የኢትዮጵያንም የተወሳሰቡ ፖለቲካዊና ታሪካዊ እውነታዎች መረዳት፤ በግል የማይመቹንንም አመለካከቶች ማቀፍ እንደሚያስፈልገው በቅጡ እንዳልተረዳች ያሳብቃል፡፡ ልምድና እድሜ፡፡

3-  ወ/ት ብርቱካን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አባል ማንነት፤ ምንነት፤ ጾታ፤ እድሜ፤ ዜግነትም መከታተል፤ ፓርቲዎቹን መቆጣጠር፤ በማቋቋሚያ አዋጁና በፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ የተዘረዘረ፤ የምርጫ ቦርድ ተቋም ሀላፊነትና ስልጣን እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ነገር ግን፤ ይሄንን የጃዋርን ዜግነት በተመለከት እንድትከታተሉና እንድታፋጥጡት መነሻችሁ ምንድነው ስትባል፤ ድርጅቱ ኦፌኮ በመገናኛ ብዙሀን በይፋ አባልነቱን ስላወጀ፤ ያንን መነሻ አድርገን ነው ስትል መልሳለች፡፡ ብዙ ፈተና ለሚጠብቀው፤ ገለልተኛነቱ ጥያቄ ውስጥ ላለ፤ በክር ላይ ለሚራመድ ተቋም፤ ይሄ መጥፎ መነሻ ነው፡፡ ምክንያም አዋጁ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት ምርጫ ቦርድ እንዲህ አይነቱን የማፋጠጥ ሂደት እንዲጀምር እንደሚያዝ ወይም እንደሚያስገደድ አይገልጽም፡፡

4-  ምርጫ ቦርድን የሚያህል የአንድን አገር ምርጫ የሚዳኝና የሚያስፈጽም ድርጅት፤ ዜና እየለቃቀመ ምርመራና ክትትል የሚጀምር ከሆነ፤ ስራው ከባድ ይሆናል፡፡ ይሄንን; መገናኛ ብዙሀን የሚዘግቡትን ዜና ተከታትለን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከቱትን አዋጅ/ጆችን እናስፈጽም የሚል መንገድ ከጀመረው፤ ስራውን መጀመር ያለበት፤ ራሱን ገዢውን ፓርቲ በመመርመርና በመገሰጽ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ፤ መገናኛ ብዙሀንን ያላግባብ ይጠቀማል፤ በመንግስት ገንዘብ ወይንም የገንዘብ ምንጩ ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ ስብሰባዎችንና ስልጠናዎችን ያካሂዳል፡፡ የመንግስት ድርጅቶችን ለስብሰባና ለስልጠና ይጠቀማል፡፡ በቅርቡ፤ መንግስት; ከሌሎች ፓርቲዎች፤ የንግዱን ማህበረሰብ እያስገደደና እያስፈራራ ገንዘብ ይሰበስባል የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ስብሰባዎች ያደናቅፋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፊርማዎችና ሰነዶች ይዘርፋል፤ ያስዘርፋል፡፡ ስብሰባዎችናና ሰልፎችን ይከለክላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከተው አዋጅ ደህንነቶች የፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ቢከለክልም፤ እስካሁን ድረስ፤ ከፓርቲው አባልነት መልቃቀቸው የማይታወቅ የኦህዴድና የብአዴን አባላት (የብልጽግና) የደህንነቱን መስሪያ ቤት ይመሩታል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፤ የፓስፖርት ምርመራ ከተጀመረ፤ ጃዋር ስለብርሀኑ ነጋ ፓስፖረት የጠቀሰው የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ አለ፡፡ ነገሩ፤ የት ጋር እንደሚቆም እንጃ፡፡

የብርቱካን ምሳሌዎችና ሌሎች ነጥቦች ስለምርጫ ቦርድ፤

5-  ምርጫ ቦርድ በዚህ ከጃዋርና ኦፌኮ ጋር በገጠመው እሰጥ አገባ ጉዳይ ላይ ስትጠየቅ፤ ብርቱካን፤ ጃዋርን ብቻ ነጥለው እንዳልጠየቁ፤ ስለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችም የሰጠችው ምሳሌ አያስኬድም፡፡ የከማል ገልቹና የኦነግ ድርቶች የላኳቸው የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ተወካዮች እንዲለወጡና ምርጫ ቦርድ እነዚህ ፓርቲዎች የላኳቸውን ሰዎች እንደማይቀበል የተናገረው፤ ሰዎቹ ወደምርጫ ቦድ ቢሮ ሲመጡ ወይም ከምርጫ ቦርድ ጋር በሚያገናኛቸው ስራ ላይ ሲሰማሩ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰዎች፤ የጃዋር መዝገብ ይፋ በሆነ መልኩ እነሱ ቢሮ እስኪመጣ፤ ወይንም ከሳሽ እስኪነሳ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ኦፌኮ ጃዋርን ይዞ ደጇ ካልረገጠ በስተቀር፤ ወይንም፤ ቅሬታና ክስ ከግለሰቦች ወይንም ከመንግስት አካላት ካልመጣ በስተቀር፤ ወሬ ከመገናኛ ብዙሀን ለቃቅሞ፤ ኦፌኮን ሚናህን ለይ ብሎ ማስጨነቅ የምርጫ ቦርድን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡ በስማበለው፤ ጃዋር ላይ እርምጃ መጀመራቸው፤ ጉዳዩ ህግና ስርአት የማስፈጸም ብቻ ሳይሆን፤ የፖለቲካ አጀንዳ የማስፈጸምም ያስመስልባቸዋል፡፡

6-  ምርጫ ቦርድ እያስፈጸመ ያለው፤ መንግስት ማስፈጸም ያቃተውን ወይም የፈራውን፤ ጃዋርን ከፖለቲካ ውጪ የማድረግ ሴራ ይመስላል፡፡ መንግስት ጃዋርን ፈርቶታል፡፡ መንግስት፤ ጃዋርን ፊት ለፊት ሊገጥመው አይፈልግም፡፡ መንግስትና ጃዋር ፊት ለፊት ሊጋጠሙ የሚችሉባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ነግር ግን፤ መንግስት ያንን አላደረገም፡፡ ይልቅስ፤ የምርጫ ቦርድ በዚህ በጃዋር-ኦፌኮ ውዝግብ ውስጥ መዘፈቅ፤ መንግስት እርምጃው ቅቡልነት ያለው እንዲመስል፤ መንግስት ምርጫ ቦርድን እንደሽፋን ተጠቅሞ፤ ጃዋርን ከፖለቲካ ለማግለል ጥሩና ሕጋዊ መስሎ በታየው ሴራ መሳተፍ ይመስላል፡፡ ብርቱካን፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ በዚህ ሴራ ውስጥ ዋና ተዋናይ ሆና መገኘቷ ባይገርመኝም፤ በዚህ ፍጥነትና በዚህ መልክ፤ በዚህ የዋህነት ይከሰታል ብዬ አልጠበቅኩም፡፡ ከዚህ የተሸለ ሴራ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ ጃዋርን በዚህ መልኩ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ግን ከባድ ነው፡፡ ዋጋም ያሥከፍላል፡፡ ጃዋር ያሁኑን ቦታውን በትግሉ ነው ያገኘው፡፡

7-  ምርጫ ቦርድ እንደጠበቀው፤ ጃዋር የዜግነት ማረጋገጫውን ባያቀርብ እንኳን፤ ጃዋርን በእጩነትና በመራጭነት እንዳይሳተፍ ይገድበው ይሆናል እንጂ፤ ከፖለቲካ ተሳትፎ አያቆመውም፡፡ ወትሮም ቢሆን፤ ጃዋር ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፍና ተጽእኖ ፈጣሪ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ፓስፖርትና በኢትዮጵያ መንግስት መልካም ፈቃድ አይደለም፡፡ በትግሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላም ባሉት ወራት፤ ጊዜያት፤ ጃዋር፤ ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፍ፤ በምርጫ ቦርድ ቡራኬ አይደለም፡፡ በራሱ ድፍረትና በህዝብ ድጋፍ እንጂ፡፡

የብርቱካንና የመንግስት ሴራ፤ የምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ

8-  ጃዋርን ከፖለቲካም ከአገርም ለማስወጣት; በምርጫ ቦርድ በኩል ዞሮ መምጣት፤ ይሄንን ያህል ጊዜ መውሰድም አያስፈልግም ነበር፡፡ ጃዋር ቢወደውም ባይወደውም፤ ቢጫንበትም ባይቀበለውም፤ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በምርጫና በእምነት፤ በትውልድም ኦሮሞ ነው፡፡ በምርጫና በፓስፖርት አሜሪካዊ ነው፡፡ የአገሮች ሁሉ አንዱ የእለት ተእለት የሉአላዊነት መገለጫ ወደአገራቸው የሚገባውን ሰው መምረጥ መቻላቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፤ ጃዋርን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት፤ ምክንያት ሁሉ አያስፈልገውም፡፡ ሟቹ መለስ ዜናዊ እንዳሉት፤ የውጭ ዜጎችን ያይናችኁ ቀለም አላማረንም ብለን ማባረር እንችላለን፡፡ መንግስት ልብ ካለው፤ ያንን በራሱ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድን እዚህ ውዝግብ ውስጥ መክተት፤ ምርጫ ቦርድም፤ ዜና ሰምቶ፤ አገኘሁት ብሎ፤ ቸኩሎ እዚህ ውስጥ መሰንቀሩ፤ ስህተት ነው፡፡

9-  የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለኢትዮጵያዊያነ ብቻ የተገደበ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህግ ይደነግጋል፡፡ ከዚያ ውጪ አዋጆቹ፤ ምርጫ ቦርድ፤ በራሱ አነሳሽነት የውጭ ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መሳተፋቸውን ሲሰማ፤ ለይቶ ምርመራ ያደርጋል አይልም፡፡ አዋጆቹን ተመልክቼ ወደዚህ ወደምርጫ ቦርድ ሰሞንኛ ድርጊት ሊጠጋጋ የሚችል ያገኘሁት አንቀጽ፤ በፓርቲ ምዝገባ ፊርማ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ያልተመዘገበን ወይም የሌለን ሰው እንደተመዘገበ አድርጎ መጓዝ በጠቋሚዎች መነሻነት ወይም በራሱ በምርጫ ቦርድ መነሻነት ምርጫ ቦርድ ሊያጣራና እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል የተደነገገው ነው፡፡ ኦፌኮ የቆየ ፓርቲ ከመሆኑም አንጻር፤ ሁለተኛም፤ ኦፌኮ ምናልባትም ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ጃዋርን ማርከናል ይበል እንጂ፤ የጃዋርን አባልነት በተመለከት ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ሰነድ ስለሌላ፤ እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ሌላ ጥቆማ ደረሰኝ ስላላለም፤ የጃዋርን ጉዳይ ለመመርመር የተነሳበት አመክንዮ ህጋዊ ጉልበት ያንሰዋል፡፡ ምናልባት ስልጣኑ አለን ካሉም እንኳን፤ ምርጫ ቦርድ ወደመገናኛ ብዙሀን ሳይሄድ ስራውን መስራትም ይችል ነበር፡፡ በተረፈ፤ የጃዋርን ጉዳይ የኦፌኮን መግለጫ ወይም ፕሮፓጋንዳ በመገናኛ ብዙሀን ሰምተን ነው መመርመር የጀመርነው የሚለው ንግግር፤ በዚህ መልክ እርምጃ የጀመሩበት ሌላ ሰው እንዳለ አይገልጽም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሕግ የማስፈጸም ወይም ስርአት የማሲያዝ ብቻ አይመስልም፡፡

10-  ነገሩ እንዲህ ነው፤ ብርቱካንና ምርጫ ቦርድ የጃዋርና ኦፌኮን የእጮኝነት ዜና ሰሙ፡፡ ምናልባትም ከመንግስት ባለስልጣናት በኩል ቀጥተኛ፤ ወይም ዘዋዋሪ፤ ጥቆማ ወይም ቅሬታ፤ ቀረበላቸው:: እርምጃ መውሰድ ጀመሩ፡፡ ብርቱካን ከጀርባ የሚገፋት ሀይል ከሌለ በቀር፤ ጃዋር ከኦፌኮ ጋር የፖለቲካ ዘመቻ ሲጀምር፤ የህዝቡን ድጋፍ ተመልክቶ፤ ኦፌኮንም ይሁን ጃዋርን መከታተልና እንዲህ ያለውን ማረጋገጫ አምጡ ማለት፤ ጃዋርን ለይቶ ከማሳደድ አይለይም፡፡ ምርጫ ቦርድ ይሄንን እንደጥሩ መነሻ መስዶ ውጭ ዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ በተመለከተ ማብራሪያ ወይም ማሳሰቢያ ማውጣት ሲችል፤ ጃዋርን ብቻ ነጥሎ መከታተሉ አግባብነት የለውም፡፡ የተአማኒነት ግንባታ ሂደቱን ያሰናክለዋል፡፡ ለይሉኝታ ሲል እንኳን፤ ከአንድነት ሀይሉ ሌላም ሰው ደብለቅ ቢያደርግና ቢመረምር፤ እንዴት ያለ ብልጠት ነበር፡፡

ጉዳዩ ጥንቃቄ ይሻል፤

11-  ምርጫ ቦርድ አለማዳላት ብቻ ሳይሆን፤ የሚያዳላ መምሰልም የለበትም፡፡ ገለልተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ገለልተኛ አይደለም ወይም አይመስልም የሚያሰኝ ሂደት ውስጥ መሳተፍም የለበትም፡፡ በዚህ በጃዋር ጉዳይ ምርጫ ቦርድ የተዘፈቀበት ነገር፤ እነዚህን መርሆች የሚጥስ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ እጁን ተጠምዝዞ ካልሆነ በስተቀር፤ ወይንም ስለጃዋር የሚጋራው የቆየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ወይም አተያይ ከሌላ በስተቀር፤ የጃዋርን የዜግነት ጉዳይ የሚያሳድድበት የሕግና ስረ-ነገር ጠባብ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ ጉዳዩን የሕግ ብቻ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ፤ ምርጫ ቦርድ

አስቀድሞ ይሄንን ማድረጉ፤ በኋላ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ጃዋርን ከእጩነት ከልክሎ ከሚመጣው ተቃውሞ ያድነዋል የሚል ክርክር ያሰማሉ፡፡ ምርጫ ቦርድ ሁለቱንም ጉዳዮች ጃዋርን ሳይነጥል፤ ለሁሉም የውጭ ዜግነት ላላቸው ኢትዮጵያዊያን በሚሰራ መልኩ ማበጀት ይችል ነበር፡፡

12-  ጃዋርን በዜግነቱ ምክንያት ከአገርም ይሁን ከፖለቲካ ማስወጣት ካስፈለገ፤ ያንን ሊያደርግ የሚችለውም የሚገባውም ስራ አስፈፃሚው የመንግስት አካል ነው፡፡ እንጂ፤ ምርጫ ቦርድ አይደለም፡፡ ጃዋር፤ በዜግነቱ ምክንያት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ምርጫ እንዳይወዳደር፤ በይፋ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ወይም አባል እንዳይሆን የሚያግደው ሕግ አለ፡፡ ጃዋር በመገናኛ ብዙሀን የኦፌኮ አባል ሆኛለሁ ስላላና ኦፌኮም አባላችን ነው ስላለ ብቻ፤ ያ በርግጥም ሕጋዊ የኦፌኮ አባል አያደርገመው፡፡ ያ የኦፌኮና የጃዋር መግለጫ፤ ፖለቲካዊ እንጂ ሕጋዊ ፋይዳ የለውም፡፡ የውጭ ፓስፖርት ይዘው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚፈተፍተው ጃዋር ብቻ አይመስለኝም፡፡ ምርጫ ቦርድ ይሄንን የጃዋርን የኦፌኮ ፓርቲ አባልነት ዜና እንደሰማ ማድረግ የነበረበት፤ ሁሉንም መሰል ሰዎች የሚመለከት መግlጫ፤ ወይም ትእዛዝ፤ ወይንም መመሪያ ማውጣት ነበር፡፡ ጃዋርን ነጥሎ በማጥቃቱ፤ ምርጫ ቦርድ ክፉኛ ተሸውዷል፡፡ ወይንም የምርጫ ቦርድ አካሄድ በከረመና እነጃዋር በሚታገሉት የቆየ፤ ለአንድ ቡድን ባለ ድብቅ ጥላቻ፤ ወይንም ለአንድ አስተሳሰብ ወይም ርእዮተአገር ባለ ጥልቅ ፍቅር የተቃኘ ወይም የተቀፈደደ አካሄድ ነው፡፡

13-  ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ላይ እንጂ፤ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዮች እየለቃቀመ መጠመድ የለበትም፡፡ ምርጫ ቦርድ ከሕግ-ነክ ጉዳዮች ወጥቶ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ከተዘፈቀ፤ ወይንም በሕግ ሽፋን፤ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን ብያኔዎችን መስጠት ከጀመረ፤ ያ የተቋሙን ተአማኒነትና ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ በጃዋር ጉዳይ የሆነው ያ ነው፡፡

14-  ምርጫ ቦርድ ከዚሀ አጣብቂኝ ለመውጣት ምን ማድረግ አለበት? ጉዳዩን፤ ከጃዋር ጉዳይነት አውጥቶ፤ ሁሉንም የውጭ ዜግነት የያዙ ፖለቲካኞች የሚመለከት እንደሆነ በማሳሰብ፤ ከግለሰባዊ ጉዳይ ወደአገራዊ ጉዳይ እና ተግዳሮት በመለወጥ፤ ከዚህ አጣብቂኝ ማምለጥ ይችላል፡፡ ምርጫ ቦርድ፤ በአዋጁ በተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት መሰረት፤ ሁሉም ፓርቲዎች የአባላትን ዝርዝር እንዲያቀርቡ ያወጣውን መመሪያ አጠናክሮ በመቀጠል፤ ጃዋርን በተናጠል ማጥቃቱን መተው አለበት፡፡ የጀመረው፤ ጃዋርን ብቻ ነጥሎ ማጥቃት አካሄድ ምርጫ ቦርድንም አገሪቱንም አላስፈላጊ ፈተና ውስጥ ይከታል፡፡ በተረፈ፤ በዚህ ሰዓት፤ ጃዋርን መግፋት አያዋጣም፡፡ ማቀፍ እንጂ፤ Engage him !! ወይም ዜግነቱ ይሰጠውና/ይመለስለትና፤ እሱ አልፍ አልፎ እንደሚያደርገው፤ በርግጫ ሳይሆን፤ በምርጫ ይዋጣልን፡፡ ብርሀኑ ነጋ የኤርትራን ፓስፖርት የተጠቀመው ለትግሉ ከሆነ፤1 የጃዋር የአሜሪካ ፓስፖርትም ለትግል የተወሰደ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም፡፡

የካቲት፤ 2012፤ ይቀጥላል …

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here